አይሁዶች በቁርአን

M. J. Fisher, M.Div

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

መግቢያና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ንፅፅር

ቁርአን ስለ አይሁዳውያን ያለው አመለካከት ትኩረትን የሚስብ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም በሙስሊሙ ዓለምና በእስራኤል መንግስት መካከል ያለው ግንኙነት በመላው ዓለም ውስጥ የውጥረት ማዕከል ነውና፡፡ እነዚህ ሰባ አንድ የቁርአን ጥቅሶች ስብስብ፣ እስልምና የአይሁድ ሕዝብን አስመልክቶ ስላለው አዎንታዊና አሉታዊ ነገሮች ይናገራሉ፡፡

መሐመድ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ውስጥ ሁሉ በሙስሊሞችና በአይሁዶች መካከል ጠላትነት ይታይ ነበር፡፡ መሐመድ እራሱን ይመለከት የነበረው ከአብርሃም፣ ከሙሴ እና ከንጉሱ ዳዊት ጋር እኩል አድርጎ ነበር፡፡ እሱም እንደ ነቢይ የተቀባይነትን ዋጋ ሊያገኝ ይችል የነበረው በመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ላይ ከተደገፈ ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ሆኖበት የነበረውም ነገር የአረቢያ ፔኒንሱላ አይሁዶች ስለ እሱ የነበራቸው አመለካከት ነበር፡፡ እነሱም እሱን የተመለከቱት በአጋንንት የተያዘ የሐሰት ነቢይ አድርገው ነበር፡፡ ሙስሊሞቹ  የንግድ ሸቀጥ ተጓዞችን ወደ መዝረፍና የሚቃወሙዋቸውንም ወደ ማጥቃት በዞሩበት ጊዜ፣ በጣም ጥቂት የነበሩት የአይሁድ ማህበረሰብ በእስላሞች ተፅዕኖ ስር መውደቃቸውን ለመቋቋም ሙከራዎችን አደረጉ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፡፡ ብዙዎቹም ልክ በመዲና እና በአን-ናዲር እንደነበሩት አይሁዶች ተጠቁና ከመሬቶቻቸው ላይ ተባረሩ፡፡ ምርታማ የነበረውም የእነሱ የፍራፍሬ ቦታዎች ለሙስሊሞች ተሰጡ፡፡ ባኑ-ቋራዛህ ከሚባለው ከአንድ የአይሁድ ማህበረሰብ ብቻ 600 ወንዶች በመገደላቸው መበለቶቻቸውና ልጆቻቸው ለሙስሊም ተዋጊዎቹ ዕቁባቶችና ባሪያዎች ተደርገዋል፡፡

እስካሁን ድረስ በአጭሩ ያየነው በአዕምሮአችን እንዳለ ከሆነ - እዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ጥቅሶች ለምን አዎንታዊ እንደሆኑና የአይሁድን ውርስ ለምን እንደሚደግፉ ለመረዳት በጣም ቀላል ይሆንልናል፣ ለዚህም ዋናው ምክንያት መሐመድ ተቀባይነቱን (ታማኝነቱን) ይገነባ የነበረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለነበረ ነው፡፡

ሆኖም ሌሎቹ የዚህ ምዕራፍ ጥቅሶች አሉታዊዎች ናቸው፣ ይህም አይሁዶቹ መሐመድን እንደ ነቢይ ባለመቀበላቸው የተሰጡ ናቸው፡፡ ቁርአን በአዎንታዊው ጎኑ የሚቀበለው አይሁዶች ያላቸው የቅዱስ መጽሐፍ ከእግዚአብሔር የመጣ መሆኑን ነው፣ ማለትም አይሁዶች እንዲያጠኑት እና የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንዲጠብቁ ያዛቸዋል፡፡ ቁርአን አይሁዶች የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ እንደሆኑ ይቀበላል፣ እነሱም ነቢይነትን እንዲሁም የእስራኤልን ምድር ወይንም የተስፋይቱን ምድር እርስት ተደርጎ እንደተሰጣቸው ይቀበላል፡፡ እንዲሁም ቁርአን ለአይሁዶች የዘላለም ሽልማትንም ያረጋግጥላቸዋል፡፡

በመሐመድ ለአይሁዶች የተሰጣቸው ይህ ሁሉ እውቅና አይሁዶችን በመሐመድ እንዲያምኑት ዘንበል አላደረጋቸውም ነበር፡፡ ስለዚህም አሉታዊ የሆኑት ጥቅሶች አይሁዶች ግብዞች ናቸው፣ ሎጂካዊ አይደሉም፣ ክፉዎች ናቸው ልበ ደንዳኖች ናቸው፣ የነቢያት ነፍሰ ገዳዮች ናቸው እናም ቅዱስ መጽሐፋቸውን አላግባብ ወክለዋል በማለት ይናገራሉ፡፡ መሐመድንና ቁርአንን አንቀበልም ካሉ የሲኦል እሳት እንደሚቀበሉም ያስጠነቅቃቸዋል፡፡

ስለዚህም ቁርአን እንደሚከተለው ይናገራል፡-

ቅድስ አገር ተሰጥቷቸዋል፡- እናንተ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች፣ ነገስታትና ነቢያት ይመጣሉ በማለት ለሕዝቡ ትንቢት የተናገረውን የሙሴን ቃሎች አስታውሱ፡፡ ሙሴ ለአይሁዶች ወደ ቅድስቲቱ አገር እንዲገቡ ነግሯቸዋል ይህም አላህ ለእነሱ ያዘዘው ነው፡፡ እነሱም በአገሩ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች በጣም ፈርተው ስለነበር አላህ ለአርባ ዓመታት ከቅድስቲቱ አገር ለይቷቸው ነበር እነሱም አገር አልባ ሆነው ተንከራተዋል 5.19-26፡፡

እግዚአብሔርን በግል ማወቅ፡- አንድ አምላክ ብቻ ነው ያለው፡፡ ክርስትያኖችና አይሁዶች የራሳቸውን ወንድ ልጅ እንደሚያውቁት አድርገው እግዚአብሔርን ያውቁታል፡፡ ሌሎች ግን ጣዖታትን በማምለክ ነፍሶቻቸውን አጥተዋል እነሱም ስለ አላህ ውሸትን ፈጥረዋል፣ ይህም የኃጢአት ስራና መገለጥን መካድ ነው 6.20-22፡፡ (ይህንን ጥቅስ በተመለከተ አዘጋጁ የሰጠውን ተጨማሪ ማብራሪያ በመጨረሻ ይመልከቱ)፡፡

ለአይሁድ ሽልማት ይጠብቃቸዋል፡- ሙስሊም የሆኑት እነዚያ፣ አይሁዶች ክርስትያኖች እና ሳባውያን በጌታቸው ዘንድ የሚጠብቃቸው ሽልማት አላቸው ስለዚህም በመጨረሻው ቀን በአላህ በማመናቸው ምንም ማዘንና መፍራት የለባቸውም ስለዚህም ትክክል የሆነውን አድርጉ 2.62፡፡

የተመረጡ ሕዝብ፡- የእስራኤል ልጆች በአላህ ተመርጠዋል እናም ከፍጥረታት ሁሉ ይልቅ የበላዮች ተደርገዋል 2.47፡፡

የአላህን በረከቶች አስታውሱ፡- መናና ድርጭቶች ለአይሁዶች ምግብ ይሆኑ ዘንድ ከሰማይ ይላክላቸው ነበር፡፡ ሙሴም ዓለቱን በመታው ጊዜ ለአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች መጠጥ ይሆን ዘንድ አስራ ሁለት ምንጭ ፈልቆላቸው ነበር 2.57-60፡፡

ቅዱስ መጽሐፍት አላቸው፡- የእስራኤል ልጆች ያላቸውን የቅዱሳት መጽሐፍቶቻቸውን የሚያረጋግጠውን ቁርአንን መቀበል አለባቸው፡፡ ስለዚህም እስልምናን የማይቀበሉ የመጀመሪያዎቹ አትሁኑ 2.41፡፡ አይሁዶችም በቅዱስ መጽሐፋቸው ውስጥ የሚያነቡትን ነገር መታዘዝ አለባቸው 2.44፡፡

የብጫዋ ላም (የአማርኛው የዳለቻዋ ላም ይላል) ቃል ኪዳን፡- ሙሴ ላምን መስዋዕት እንዲያደርጉ ሕዝቡን ባዘዘ ጊዜ እሱ የሚቀልድባቸው መስሏቸው ያስቡ ነበር፡፡ ሕዝቡም በአንድ ጥያቄ ሙሴን ፈተኑት ይህም መስዋዕት ተደርጋ የምትታረደውን የላሟን ተፈጥሮ በተመለከተ ነው፡፡ ዕድሜዋ መካከለኛ፣ ከለሯ ደማቅ ቢጫ፣ ጤናማና ምንም እንከን የሌለባት እንድትሆን ተወስኖ ነበር፡፡ አይሁዶቹም በመጨረሻ የታዘዙትን እንዲያደርጉ ታዘዘው ነበር ነገር ግን አላደረጉትም 2.67-71፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በአይሁዶች ይጠና ነበር፡- ቅዱስ መጽሐፍትን የወረሱት እነዚያ በሚገባ  አጥንተዋቸዋል እንደዚሁም ስለ አላህ መባል የሌለበትን እና እውነት ያልሆነው ነገር ያውቃሉ 7.169፡፡ አንድ ቅዱስ መጽሐፍን ቢያጠኑም እንኳን ክርስትያኖችና አይሁዶች አይስማሙም 2.113፡፡

እስልምናን አንቀበልም በማለት ግንባር ቀደሞች፡- ከቅዱስ መጽሐፋችሁ ጋር ይስማማልና ቁርአንን አንቀበልም በማለት ግንባር ቀደሞች አትሁኑ፡፡ አላህን ፍሩ! በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ላላችሁ እውነት ቅኖች ሁኑ ለትንሽ ዋጋም አትሽጡት እውነትንም ከውሸት ጋር አትቀላቅሉ ወይንም እውነትን አትደብቁ፡፡ ከሙስሊሞች ጋር አምልኩ ለድሃዎች የሚያስፍልጋቸው እንዲሰጣቸው ስጦታን ስጡ ደግሞም ፀልዩ 2.41-45፡፡

የክርስቶስ ስቅለት፡- አይሁዶች ቃል ኪዳንን አፍርሰዋል የኣላህንም መገለጥ ክደዋል ነቢያቶችንም በስህተት ገድለዋል፡፡ በማርያምም ላይ ክፉ የሆነን ስድብ ይናገራሉ፡፡ እንደዚሁም ኢየሱስን የማርያም ልጅና የአላህን መልእከተኛ ገደልነው ይላሉ፡፡ አልገደሉትም አልሰቀሉትምም፡፡ ነገር ግን ለእነሱም መስሎ ታያቸው እንጂ፡፡ አልገደሉትም ነገር ግን አላህ እሱን ወደ እራሱ ወሰደው 4.155-158፡፡

አይሁዶችና ቅዱስ መጻሕፍት፡- የአይሁድ ሕዝብ ቶራህ ተሰጥቷቸው ነበር (የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ አምስት መጻሕፍት) ነገር ግን ለእሱ ታዛዦች አልነበሩም፡፡ እነሱም ከባድ መጽሐፍትን የተጫነች አህያን ይመስላሉ፡፡ የአላህን መገለጥ በመቃወማቸው እነሱ አስፀያፊዎች ናቸው 62.5፡፡ የእስራኤል ልጆች መጽሐፍ ቅዱስ፣ ነቢይነት እንዲሁም ከሌሎች ሕዝቦች ይልቅ ሞገስ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ በወረደላቸው ጊዜ ግን እነሱ ተከፋፈሉ 45.16-17፡፡ ለሙሴና መጽሐፍ ቅዱስን ለወረሱት ለእስራኤል ልጆች ምሪት ተሰጥቷቸው ነበር፣ መጽሐፉም ለባለአዕምሮዎች ምሪትን የሚሰጥ ነበር 40.53-54፡፡ እነሱም የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል አጣመሙ ከዓውዳቸውም ውጭ ወሰዷቸው፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉ  የማይታመኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ እለፋቸው (ታገሳቸው) ይቅርታም አድርግላቸው አላህ መልካም ሠሪዎችን ይወዳልና 5.13፡፡

አዳኝ የላችሁም፡- እናንተ አይሁዶች ከፍርድ ቀን እራሳችሁን ጠብቁ ያን ጊዜ አዳኝ፣ አማላጅ ወይንም ለኃጢአቶቻችሁ ቤዛ የሚሆንላችሁ የላችሁም 2.47-48፡፡

ያለፈውን ስህተቶቻችሁን አስታውሱ፡- አላህ ለሙሴ መጽሐፍ ቅዱስን ከሰጠው በኋላ፣ አባቶቻችሁ እንዲያመልኩት የወርቅን ጥጃ ሠሩ፡፡ ስለዚህም ሙሴ አይሁዶችን እራሳቸውን እንዲገድሉ አደፋፈራቸው፡፡ እነሱም በመብረቅ ተመቱ ነገር ግን በተዓምራት እንደገና በሕይወት ቆሙ 2.53-56፡፡

የነቢያት ገዳዮች፡- አይሁዶች በአላህ መገለጥ ባለማመን ነቢያትን በዓመፅ ገደሏቸው፡፡ እነሱም ውርደትን ጉስቁልናን ተቀበሉ፣ እንዲሁም ተረገጡ፡፡ የአላህንም ቁጣ ተቀበሉ 2.61፡፡ የማርያም ልጅ ኢየሱስ ተዓምራትን ለማድረግ ኃይልን ተሰጥቶ እና በመንፈስ ቅዱስም ተበረታትቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው በማያስደስታቸው ትምህርት በመጣባቸው ጊዜ አይሁዶች ትዕቢትን ተሞሉ አንዳንዶችም አስተባበሉ ሌሎችንም ገደሉ 2.87፡፡ መሐመድንም ከማመናችሁ በፊት ማረጋገጫ እንዲሆንላችሁ ከሰማይ ምልክትን እንዲሰጣችሁ ጠየቃችሁት፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ብርሃንን በሚሰጠው በቅዱስ መጽሐፍት ውስጥ ታላላቅ ምልክቶችን ሰጧችሁ እነሱን ለምን ገደላችኋቸው?

ሰንበትን ሻሪዎች ወደ ዝንጀሮነት ተቀይረዋል፡- አይሁዶች ማስታዎስ ያለባቸው ሰንበትን ያልጠበቁት አይሁዶች ወደ አስቀያሚ ዝንጀሮነት በኣላህ እንደተቀየሩ ነው ይህም ለሚመጣው ትውልድ ምሳሌ የሚሆን ነው 2.65-66፡፡  

ልበ ደንዳኖች፡- አላህ የሞተን ሰው ሕይወትን ቢሰጠውም እንኳን የአይሁዶች ልብ ደርቆ (ደንድኖ) እናም ከድንጋይም ይልቅ ጠንክሮ ነበር 2.72-74፡፡

ግብዞች፡- እነሱም መንግስተ ሰማያት እንደሚገቡ እንደሚያምኑ ይናገራሉ ነገር ግን እነሱ በእርግጥ ለመሞት የሚፈልጉ መሆናቸውን በእርግጥ የሚያምኑ ቢሆን፡፡ በእርግጥ እነሱ የዚህን ዓለም ሕይወት ይወዳሉ ይህም ፓጋኖች እንኳን ከሚያደርጉት በላይ ነው እንደዚሁም ሞትን ይፈራሉ ምክንያቱም የሚያጋጥማቸውን ፍርድ ምን እንደሆነ ያውቃሉና 2.94-96፣ 62.6-8፡፡

አይሁዶች ጠላቶች ናቸው፡- በጣም ጠንካራ የእስልምና ጠላቶች አይሁዶችና ፓጋናች ናቸው፣ ነገር ግን በጣም ጥሩና ተወዳጆች የሆኑት እራሳቸውን ክርስትያኖች ነን በማለት የሚጠሩት ናቸው፡፡ እነሱም ቀሳውስትና መነኮሳት አሏቸው እነሱም የማይኮሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ቁርአን ሲነበብ በሚሰሙበትም ጊዜ እንባ ከአይኖቻቸው ይፈሳል ምክንያቱም እውነት እንሆነ ያውቃሉና፡፡ ነገር ግን እነዚያ የማያምኑቱ እና የአላህን መገለጥ የሚክዱቱ ወደ ሲዖል እሳት ውስጥ ነው የሚሄዱት 5.82-86፡፡

ገነትን መጠየቅ፡- አይሁዶችና ክርስትያኖች የሚናገሩት እነሱ ብቻ ገነት እንደሚገቡ እንደሚፈቀድላቸው ነው፣ ይህም ከንቱ ምኞታቸው ነው 2.111፡፡

አይሁዶችን ጓደኛ ማድረግ ክልክል ነው፡- ክርስትያኖችን ወይንም አይሁድን ጓደኛዎች የሚያደርጉ ሙስሊሞች ከእነሱ እንደ አንዱ ናቸው 5.51፡፡

አይሁዶች ከፍጥረት ሁሉ ክፉ ናቸው፡- ክርስትያኖች አይሁዶች እና ጣዖታትን አምላኪዎች በመሐመድና ወይንም በቁርአን የማያምኑቱ ለዘላለም በእሳት ውስጥ ለመቃጠል ይሄዳሉ እናም በምድር ላይ እጅግ በጣም ክፉ የሆኑ ፍጥረታት ናቸው 98.6፡፡

አይሁዶችን ተዋጉዋቸው፡- ሙስሊሞች እስልምናን የሚቃወመውን ማንኛውንም ሰው  ክርስትያኖችንም አይሁዳውያንንም ይዋጋሉ፡፡ እነሱ መደበኛ የገንዘብ ክፍያ እስካላደረጉላችሁ ድረስ እራሳቸውንም ሙሉ ለሙሉ ለእስልምና ተዋጊዎች እስካላስገዙ ድረስ ተዋጉዋቸው 9.29፡፡

የአዘጋጁ ተጨማሪ ማብራሪያና ማሳሰቢያ

ክርስትያኖችና አይሁዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ እግዚአብሔርን እንደሚያውቁት የተጠቀሰበትን ምዕራፍ 6.20 ላይ ያለውን    ሐሳብ የአማርኛው ቁርአን ያስቀመጠው እንደሚከተለው ነው፡- ‹እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (መሐመድን) ያውቁታል፣ እነዚያ ከነርሱ ውስጥ ነፍሶቻቸውን ያከሰሩት እነርሱ አያምኑም፡፡› በማለት አማኞቹ አይሁዶች መሐመድን እንደሚያውቁት ተደርጎ በቅንፍ ተቀምጧል፡፡ የዚህ ገፅ አዘጋጅ አስሩንም ልዩ ልዩ የቁርአን ትርጉሞችን አነፃፅሮ የሚከተለውን አግኝቷል፡፡ ፒክታል የሚባለውና የታወቀው ትርጉም ያስቀመጠው ‹ይህንን መገለጥ ያውቁታል› በማለት ነው፡፡ የዩሱፍ አሊ ትርጉም ‹ይህንን ያውቃሉ› ብሎታል፡፡ የሂላሊ-ካን ትርጉም ደግሞ ቅዱስ መጽሐፍ የወረደላቸው አይሁዶችና ክርስትያኖች ናቸው በማለት በቅንፍ አስቀምጦ ያውቁታል ለሚለው ደግሞ ልክ እንደ አማርኛው ትርጉም ‹መሐመድን› ብሎታል፡፡ የ ሻኪር ትርጉም ‹እሱን› ያውቁታል በማለት አስቀምጦታል፡፡ የሺር አሊም ትርጉምም እንዲሁ ‹እሱን ያውቁታል› ይላል፡፡ የካሊፋ ትርጉም ‹ይህንን ያውቁታል› ሲል፣ የአርበሪ እና የፓልመር ትርጉሞች ‹እሱን ያውቁታል› ይላሉ የሮድዌል ትርጉም ደግሞ ‹እሱን ያውቁታል የሚለውን አስቀምጦ በቅንፍ ‹መሐመድን› ሲል የሴል ትርጉም በድፍኑ ‹ሐዋርያችንን ያውቁታል› ይላል፡፡ ከዚህ በላይ የዘረዘርኳቸው አስር የቁርአን ልዩ ልዩ ትርጉሞች መኖር ምን ያመለክታል? የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመልከት ለሌላ ጊዜ ጽሑፍ አስተላልፌዋለሁኝ፡፡ ይህንን ማለት ያስፈለገኝ ብዙ ሙስሊሞች የክርስትያን መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ትርጉም፣ የእነሱ ቁርአን አንድ ብቻ እንደሆነ ደጋግመው ስለሚናገሩ ጉዳዩ በስፋት ሊመረመር ያስፈልገዋልና ነው፡፡

ሆኖም ግን በዚህ ምዕራፍ 6.20 መሠረት ሦስቱ ትርጉሞች ‹ይህንን›፣ ሁለቱ ትርጉሞች ‹መሐመድን› አንዱ ደግሞ ‹ሐዋርያውን› ሲሉ አራቱ ‹እሱን› ይላሉ፡፡ ቁርአን 6 ቁጥር 20 ከቁጥር 19 ጀምሮ አውዱን ጠብቆ ሲነበብ አይሁዶችና ክርስትያኖች እርሱን ያውቁታል የሚለው ሐሳብ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሔርን ያውቁታል ማለት ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ‹ይህንን› የሚሉት ሦስቱ ትርጉሞችና ‹እሱን› የሚሉት አራቱ ትርጉሞች ከቁጥር አስራ ዘጠኝ ጀምሮ ተያያዘው ሲነበቡ የሚሰጡት ትርጉም ‹እግዚአብሔርን› ያውቃሉ የሚል ነው፡፡ ስለዚህም ‹መሐመድን› እንዲሁም ‹ሐዋርያችንን› የሚሉት የሌሎቹ ሦስት ትርጉሞች ከአማርኛው ቁርአን ጭምር ያስቀመጡት ሐሳብ የተሳሳተና የሚያሳሳት የዓውዱንም የሐሳብ ፍሰት ያልተከተለ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የአማርኛው ቁርአን ‹እሱን› የሚለውን ጭራሽ ስላጠፋውና መሐመድን በቅንፍ በማስቀመጡ በጥቅሉ ቁጥር ሃያን ትርጉም የሌለው ያደርገዋል፡፡ የሆነው ሆኖ ቁርአን አይሁዶች፣ አንድ ሰው ልጁን እንደሚያውቀው አድርገው እግዚአብሔርን ያውቁታል በማለት መናገሩ የአይሁዶችና የክርስትያኖች እምነት የሚያልኩትን አምላክ በትክክል እና በተጨባጭ በማወቅ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያሳያል፡፡

ይህንን ጽሑፍ የምታነቡ ሙስሊሞችን ሁሉ የዚህ ገፅ አዘጋጆች በክርስቶስ ፍቅር የሚጠይቋችሁ ልባችሁን አስፍታችሁና በማስተዋል ሆናችሁ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታነቡ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ያለምንም የሐሳብ መፋለስ እና ግራ መጋባት የሚያስተላልፈው መልእክት የሰው ልጅ በሙሉ ኃጢአተኛ እንደሆነ፣ በኃጢአቱም ምክንያት ከእግዚአብሔር ክብርና መንግስት እንደጎደለ ደግሞም እንደራቀ ፍርድም እንደሚጠብቀው ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከፍቅሩ የተነሳ ለሰው ልጅ የደኅንነትን መንገድ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አዘጋጅቷል የሚለውን የደስታ ዜና ይናገራል፡፡ ስለዚህም ንስሐ በመግባት ወደ ጌታ ኢየሱስ የሚመጡትን እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ይቅር ብሎ እንደሚቀበላቸው ሲሆን እነሱም በሕይወታቸው ውስጥ ታላቅን ለውጥ እንደሚለማመዱ እና እንደሚያዩ እርግጠኛ ነገር ነው፡፡

እኛ አዘጋጆቹ በሕይወታችን ውስጥ ይህንን አይተነዋል፣ ጥማታችንና ፍላጎታችንም እናንተም ይህንን እንድታዩት ነው፡፡ ስለዚህም ወደ አቅራቢያችሁ የወንጌል አማኝ ቤተክርስትያን በመሄድ የጌታ ቃል ስሙ መጽሐፍ ቅዱስን አግኙና አንብቡ በንስሐም ወደ ጌታ ፊት ቅረቡ መሐሪ ነውና በክርስቶስ በኩል ይምራችኋል አሜን::

 

የትርጉም ምንጭ: The Jews, Chapter 22 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ