የቁርአን አስገራሚ ጥቅሶች

በአዘጋጆቹ

ቁርአን የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ እንደሆነ ግልጥ ነው፡፡ መጽሐፉ ስለራሱ የሚናገረው ነገር ፍፁምና ምንም ስህተት የሌለበት እና ከእግዚአብሔር የመጣ አድርጎ ነው፡፡ እንዲያውም በምዕራፍ 4.82 ላይ የሚከተለውን እናነባለን ‹ቁርአንን አያስተነትኑምን? ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር›፡፡ ይህ ጥቅስ ቁርአን ከአላህ ዘንድ ስለ ሆነ ምንም ስህተት የለበትም፣ ስህተት ቢገኝበት ግን ከአላህ ዘንድ አይደለም ማለት ነው የሚል ሐሳብን የያዘ ነው (አላህ አይሁዶችና ክርስትያኖች የሚጠሩት እግዚአብሔር እንደሆነ ተደርጎ ተቆጥሮ ማለት ነው)፡፡ ቁርአን እራሱ በሚሰጠው ማስረጃ መሠረት ከእግዚአብሔር አለመሆኑ በጣም ግልጥ ነው፡፡ እጅግ በጣም ብዙ ከሆኑት ማስረጃዎችም መካከል የሚከተሉት አስገራሚ ነገሮች በመጽሐፉ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አስገራሚ ነገሮች በማስተዋል ሲታዩ ቁርአን ከእግዚአብሔር ነው የሚለውን አባባል ሁሉ ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ይጥሉታል፡፡ እነዚህ አስገራሚ ነገሮች ምንድናቸው፤ በመለኮታዊ አሰራር ተገለጠ ከሚባል መጽሐፍ በእርግጥ ይጠበቃሉን? እስኪ የሚከተሉትን አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡-

ከዚህ በታች የተወሰዱት ጥቅሶች በሙሉ በ1997 ለሁለተኛ ጊዜ በነጃሲ ማተሚያ ከታተመው ቁርአን ላይ የተወሰዱ ናቸው፡፡

1. ወደ ቤት ውስጥ በጀርባ በኩል (በጓሮ በኩል) መግባት ጥሩ (መልካም ስራ) አይደለም ‹.... መልካም ስራም ቤቶችን ከጀርባዎቻቸው በመምጣታችሁ አይደለም ግን የመልካም ስራ ባለቤት የተጠነቀቀ ሰው ነው ቤቶችንም ከደጃፎቻቸው በኩል ግቧቸው አላህንም ፍሩ ልትድኑ ይከጅላልና (በላቸው)› 2.189፡፡ ወደ ቤቶች ውስጥ በጓሮ በኩል መግባት መልካም ስራ አይደለም ስለዚህም በጓሮ በኩል ወደቤት አትግቡ ከፊት ለፊት በኩል ግቡ የሚለው ቃል መሐመድ ከአላህ እንደመጣለት  የተናገረው ነው፡፡ ከአላህ የመጣው ይህ ቃል ከእምነት እና ከደኅንነት ጋር ምን የሚያያይዘው ነገር አለ? በእርግጥ እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነትን ነገር ይናገራልን? ወይንስ ይህ ስለምን እና በምን ምክንያት በእግዚአብሔር ስም ተነገረ? ትዕዛዙ የተሰጠው በአንድ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ወይንስ አንድ ሌላ ቤትን በእንግድነት ለሚጎበኙ ነው? በእውነት ለማነው የተነገረው? በአጠቃላይ ይህ የእግዚአብሔርና ከመጽሐፍት እናት ከሰማይ የወረደ የእግዚአብሔር ቃል ነውን? መልሱን ለአስተዋይና እውነትን ወዳጅ ለሆኑ ሙስሊም አንባቢዎች እንዲያስቡበት እንተወዋለን፡፡

2. ሰዶምና ገሞራ የተባሉት ከተሞች የተገለበጡት ቃል በቃል ከላይ ወደ ታች ነው፡፡

ሀ. ‹.... ትዕዛዛችንም በመጣ ጊዜ (ከተማይቱን) ላያዋን ከታችዋ አደረግን (ገለበጥናት) ተከታታይም የኾነን የሸክላ ድንጊያ በርሷ ላይ አዘነምን› 11.81-82፡፡ እንዲሁም ደግሞ፤

ለ. ‹.... ላይዋንም ከታችዋ አደረግን በነሱም ላይ የሸክላ ደንጊያዎችን አዘነብንባቸው› 15.74፡፡ እነዚህ ሁለት ጥቅሶች የሚናገሩት ሰዶምና ገሞራ የተገለበጡት ከላይ ወደታች ነው በማለት ነው፡፡ እነዚህን ጥቅሶች እንደ አስገራሚ ያቀረብንበት ምክንያት ታሪካዊ ማስረጃ ስለሌላቸው እና ከስማ በለው ወይንም በፈጠራ የተቀመጡ በመሆናቸው ነው፡፡ አንድ የሙስሊም አንባቢ በሰዶምና በገሞራ ከተማ ላይ ስለሆነው ነገር የሙሴን መጽሐፍ የዘፍጥረት ምዕራፍ 19 በማንበብ ምን እንደሆነ በትክክል መረዳት ይችላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ ኪዳንም ላይ በዘፍጥረት ስለሆነው ነገር በትክክል ተመሳሳይ ነገርን ይናገራል አሁንም ሉቃስ 17.29 በትክክል ይናገራል፡፡   

3. ጎበዞቹና ውሻቸው ለ309 ዓመታት በዋሻ ውስጥ ተኝተው በእንቅልፍ ነበሩ፡፡

ሀ. ‹... ... በዋሻቸውም ውስጥ ሦስት መቶ ዓመታትን ቆዩ ዘጠኝንም ጨመሩ› 18.9-25፡፡ ጎበዛዝቱና ውሻቸው በተቀመጡበት ዋሻ ውስጥ ለሦስት መቶ ዘጠኝ ዓመታት በእንቅልፍ ውስጥ ቆይተው ነቁ፡፡ አስገራሚ ከሆኑት የቁርአን ነገሮች አንዱ ለሦስት መቶ ዘጠኝ ዓመታት በዋሻ ውስጥ የቆዩት ሰዎች ታሪክ ነው፡፡ ለመሆኑ የዚህ ታሪክ ምንጩ እግዚአብሔር ነውን፣ በእውነት ይህ ታሪክ የእግዚአብሔርን ቃል መስፈርት ያሟላልን?  

4. በጭቃማ ውሃ ውስጥ የፀሐይ መጥለቅ፡፡

ሀ. ‹ወደ ፀሐይ መግቢያም በደረሰ ጊዜ ጥቁር ጭቃ ባላት ምንጭ ውስጥ ስትጠልቅ አገኛት ባጠገቧም ሕዝቦችን አገኘ ዙልቀርነይን ሆይ! ወይም (በመግደል) ትቀጣለህ ወይም በነርሱ መልካም ነገርን (መማረክን) ትሠራለህ አልነው› 18.86፡፡

በአሁኑ ጊዜ በጣም ብዙ የሆኑ ሙስሊሞች ቁርአን ሳይንሳዊ የሆኑ ነገሮችን ስለሚናገር አንዱ የእግዚአብሔር ቃል የመሆኑ ማስረጃ ነው ይላሉ፡፡ ሳይንሳዊ የተባሉትን ጥቅሶች ከጊዜ ወደ ጊዜ አንድ በአንድ ስለምንመለከታቸው አንባቢዎች እንዲከታተሏቸው እንጠይቃለን፡፡ የዚህ የቁርኣን 18.86 ጉዳይ ግን በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ይህ ክፍል ዙልቀርነይን የተባለውን ሰው አጠቃላይ ታሪክ አቅርቧል፡፡ ሆኖም አጠቃላይ ታሪኩ ሲመረመር ቁርአን ምንያህል አስገራሚ ነገሮች ያለበት መጽሐፍ መሆኑን በግልፅ ያሳየናል፡፡ የአማርኛው ቁርአን 1997ዓ.ም ሁለተኛው እትም አታሚዎች ለዚህ ጥቅስ ማብራሪያ የሚሆን የሚከተለውን የግርጌ ማስታዎሻ ሰጥተዋል ‹በዓይን አስተያየት በውሃው ውስጥ የምትጠልቅ መስላ› (ቁርአን ገፅ 207 የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 1)፡፡ ይህንን የመሰለ የግርጌ ማስታዎሻ በአረብኛውና በሌሎች የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ላይ ግን የለም፡፡ ለአማርኛ ተርጓሚዎቹም  ይህ ነገር አልዋጥና ከሳይንስም ከተፈጥሮም ጋር አልሄድ ብሏቸው ይሆን? ታዲያ ለምን ሊሸፍኑት ሞከሩ?

ለ. በዚሁ ክፍል በቁጥር 89-90 ውስጥ ዙልቀርነይን ወደ ምስራቅ እንደገና ተጉዞ ፀሐይን ስትወጣ አግኝቷታል፡፡ በመውጫዋም ቦታ ላይ የፀሐይ መከላከያ ያልተደረገላቸውንም ሰዎች አግኝቷል፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው፣ የምን ጎሳዎች ናቸው፣ አላህ የፀሐይ መከለያን ለምን አላደረገላቸውም፣ ይህስ መጻፉ እና ከአላህ ዘንድ መገለጡ ምን ትምህርትን ይሰጣል? እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለአስተዋይ አንባቢ በጣም አስገራሚዎች ናቸው፡፡ ይህስ ሳይንሳዊ የሚባል እና የቁርአንን ከእግዚአብሔር መምጣት ማስረጃ ይሆንን?     

5. በሁለት ተራራዎች መካከል የተገነባው ትልቁ የብረት ድልድይ

የዙልቀርነይን ነገር ወደ ምዕራብና ምስራቅ በመሄድ ብቻ አላበቃም ወደ ሰሜንም ተጉዞ የሚከተለውን ነገር አድርጓል፡- ‹ዙልቀርነይን ሆይ የእጁጅና መእጁጅ በምድር ላይ አበላሺዎች ናቸውና በኛና በነሱ መካከል ግድብን ታደርግልን ዘንድ ግብርን እናደርግልህን? አሉ፡፡ 94፤ .... የብረትን ታላላቅ ቁራጮች ስጡኝ (አላቸው) በሁለቱ ኮረብታዎች (ጫፍ) መካከልም ባስተካከለ ጊዜ አናፉ አላቸው (ብረቱን) እሳትም ባደረገው ጊዜ የቀለጠውን ነሐስ ስጡኝ በርሱ ላይ አፈስበታለሁና አላቸው፡፡ 95፤ (የእጁጅና መእጁጅ) ሊወጡትም አልቻሉም ለርሱ መሸንቆርንም አልቻሉም፡፡ 96፤ ይህ (ግድብ) ከጌታዬ ችሮታ ነው የጌታዬም ቀጠሮ በመጣ ጊዜ ትክክል ምድር ያደርገዋል የጌታዬም ቀጠሮ የተረጋገጠ ነው አለ፡፡ 98› በዚህ ቁጥር 98 መሠረት ይህ ዙልቀርነይን የገነባው ግድብ እስከ ጌታ ምፃት ድረስ መቆየት ያለበት ግድብ ነው፡፡

በቁጥር 94 ላይ ጁጅ ማጁጅ ተብለው የተጠቀሱትን ለማብራራት በቁርአን ገፅ 207 የግርጌ ማስታዎሻ ቁጥር 2 ላይ ‹ጎግ ማጎግ የተባሉት ሕዝቦች› እንደሆኑ ተገልጧል፡፡ ከዚህም መረዳት እንደሚቻለው ዙልቀርነይን ግድብ የሰራው ጎግ ማጎግ የተባሉትን ሰዎች ለመከላከል ነው፡፡ ታዲያ ይህ ግድብ የት ነው ያለው? ሁለቱ ተራራዎችስ ማንና ማን ይባላሉ? ግድቡ በእርግጥ ተሰርቶ ከሆነ የት ሄደ፣ የአርኪዎሎጂስ ምርመራ አረጋግጦታልን? ለዚህ ግድብ መሠራት ከቁርአን ሌላ ታሪካዊ ማስረጃ ይገኛልን፣ በታሪክስ ማረጋገጥ ይቻላልን? እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች የምንጠይቀው ቁርአንን ለማንቋሸሽ ፈልገን ሳይሆን አንባቢዎች ለዘላለም ሕይወት መዳን የሚጠቅማችሁ ምን እንደሆነ በጥንቃቄ መርምራችሁ እንድታውቁ ነው፡፡

6. ንጉሱ ሰለሞን የወፎችን ንግግር ተምሮ ነበር፡፡

‹ሱለማይንም ዳውድን ወረሰ አለም፡- ሰዎች ሆይ! የበራሪን ንግግር (የወፍን ቋንቋ) ተስተማርን ከነገሩም ሁሉ ተሰጠን ይህ እርሱ በእርግጥ ግልጽ የኾነ ችሮታ ነው› 27.16፡፡ ይህ የሰለሞን አባባል እውነትነት ካለው በመጀመሪያ መምጣት ያለበት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሰለሞን የወፍን ቋንቋ ስለመናገሩ የሚናገር የእስራኤላውያን ታሪክ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ምንም የለም፡፡ ታዲያ ቁርአን ከየት አመጣው? ሰለሞን በወፎች ቋንቋ ተናገሮ ከሆነ እስራኤላውያን ይህንን ተዓምር ስለምን አልጻፉትም መጽሐፍ ቅዱስስ ስለምን ደበቀው? ወይንስ ይህ ዝም ብሎ አፈታሪክና የፈጠራ ጭማሪ ነውን?

7. ጉንዳኖች መናገር ይችላሉ

‹በጉንዳንም ሸለቆ በመጡ ጊዜ አንዲት ጉንዳን፡- እላንተ ጉንዳኖች ሆይ! ወደ መኖሪያዎቻችሁ ግቡ ሱለማይንና ሰራዊቱ ከነርሱ የማያውቁ ሲኾኑ አይሰባብሩዋችሁ አለች› 27.18፡፡ በምዕራፍ 27 በቁጥር 19 ላይ እንደተጻፈው ደግሞ ሰለሞን ከጉንዳኗ ንግግሯ ተደንቆ ፈገግ እንዳለ እናገኛለን፡፡ ይህም አስገራሚ የጉንዳን ንግግርና የጉንዳኖች ሸለቆ ክስተት በመጽሐፍ ቅዱስም በእስራኤል ታሪክም ውስጥ የሌለ ነገር ነው፡፡ የጉንዳኗ ንግግር ሰለሞንን ማስደነቁና ፈገግ ማሰኘቱም ይገርማል፡፡ ይህንን ጥቅስ ለማብራራት ሙከራ ካደረጉት የእንግሊዝኛ ቁርአን ትርጉሞች አንዱ የቁርአን 6.143 ማብራሪያን ጠቁሟል፡፡ በማብራሪያውም ግልፅ እንደሆነው በመሐመድ ጊዜ አንድ ላም እንደተናገረችና ተዓምር እንደተባለ ደግሞም አንድ ተኩላ ስለ ነቢዩ መሐመድ ከአላህ ዘንድ መላክ ጭምር ለእረኛ እንደተናገረ ተዘግቧል [The Noble Qur'an in the English Language by Dr. Muhammad Taqi-ud al-Hilali and Dr. Muhammad Muhsin Khan page 170-171]፡፡

8. አላህ ሰባት ሰማይና ሰባት ምድርን ነው የፈጠረው፡፡

‹አላህ ያ ሰባትን ሰማያት የፈጠረ ነው ከምድርም መሰላቸውን (ፈጥሯል) በመካከላቸው ትእዛዙ ይወርዳል አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ መኾኑን አላህም በነገሩ ሁሉ በዕውቀት ያካበበ መኾኑን ታውቁ ዘንድ (ይህንንም አሳወቃችሁ) 65.12፡፡ ይህም ፍፁም እንግዳ የሆነ ነገር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሦስት ሰማይ የሚናገር ሲሆን እነዚህንም በትክክል ማስረዳት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ስለ ሦስት ወይንም ስለ ሰባት ምድር መፈጠር አሁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ምንም ነገር የለም፡፡ ቁርአን ላይ ያሉት ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መኖር አለባቸው ማለታችን አይደለም፣ መገኘትም የለባቸውም፡፡ እኛ የምንለው በቁርአን ላይ ያለው ካለፉት ቅዱሳን መጻፍት እና ከተፈጥሮ ሳይንስም ውስጥ የሌለ ነገር መሆኑን ነው፡፡   

9. ተወርዋሪ ኮከቦች ክፉ መናፍስትን ለማባረር ነው የተፈጠሩት፡፡

‹ቅርቢቱን ሰማይም በእርግጥ በመብራቶች (በከዋክብት) አጌጥናት ለሰይጣናትም መቀጥቀጫዎች አደረግናት፡፡ ለነርሱም (ለሰይጣኖች) የእሳትን ቅጣት አዘጋጀን› 67.5 ለሰይጣናት መቀጥቀጫዎች አደረግናት የሚለው በእንግሊዝኛው ቁርአን ላይ 'And indeed We have adorned the nearest heaven with lamps, and We have made such lamps [as] missiles to drive away the Shayatin [devils], and have prepared for them the torment of the blazing fire' [The Noble Qur'an in the English Language by Dr. Muhammad Taqi-ud al-Hilali and Dr. Muhammad Muhsin Khan page 625]፡፡ ይህ የቁርአን ጥቅስ በሰማይ ያሉትን ከዋክብት ሰይጣናትን ለማባረር እንደሚሳኤል አደረግናቸው ነው የሚለው፡፡ ይህም በሙስሊም የቁርአን ተንታኞች እና አስተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው የተወርዋሪ ኮከቦች መፈጠር አንዱ ዓላማ ነው፡፡ ይህንን ጥቅስ ለማብራራት ከላይ የተጠቀሰው የእንግሊዝኛ ቁርአን በምዕራፍ 85 ቁጥር 1 ላይ የተሰጠውን ትንተና ይጠቁማል፡፡ ትንተናውም የተሰጠው Sahih Al-Bukahri, Vol. 4, Chapter 3 ላይ ሲሆን በቀጥታ የሚለው ‹ከዋክብቱ የተፈጠሩት ለሦስት አላማ ነው፣ አንደኛው ሰማያትን ለማስዋብ፣ ሰይጣኖችን እንደ ሚሳይል ለመምታት፣ እና መንገደኞችን ለመምራት ነው› የሚል ነው፡፡ በመቀጠልም ‹ከዚህ ውጭ የሆነ ትርጉምን ለመተርጎም የሚሞክር ማንም ሌላ ሰው ቢኖር ተሳስቷል፣ በከንቱም ይደክማል ከተወሰነውም በላይ በማለፍ እራሱን ያስቸግራል› በማለት ይደመድመዋል፡፡

ተወርዋሪ ኮከቦች ጅኒዎችን ወይንም ሰይጣናትን ለማባረር የተፈጠሩ መሆናቸው በቁርአን ውስጥ መገለጡ በጣም አያስገርምም!

የአዘጋጆቹ ማሳሰቢያ፡-

በቁርአን ውስጥ የምናገኛቸው አስገራሚ ጥቅሶች በእርግጥም የሚያስገርሙ ናቸው፡፡ ይህ ማስገረም ዝም ብሎ ማስገረም ሊሆን አይችልም፡፡ አስገራሚ የሆኑበት ምክንያት የእግዚአብሔር ቃል ነው ተብሎ በሚጠራ መጽሐፍ ውስጥ ከእግዚአብሔር እንደመጡ ተደርገው መቀመጣቸውና መቆጠራቸው ነው፡፡ በትክክል ሲመረመሩ ግን የቅዱስ እግዚአብሔርን ባሕርያት እና ሁሉን አዋቂነቱንና ሁሉን ቻይነቱን የሚነቅፉና ለእሱ ባሕርያት ፈፅሞ የማይስማሙ ናቸው፡፡

ለዚህ ነው ቁርአን የሚያቀርበው አምላክ የክርስትያኖችን አምላክ ሊሆን አይችልም የምንለው፡፡ የክርስትያኖች አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ክቡር እና በፍትህም የማያዳላ ነው፡፡ የተናገረውና የሚናገረውም ሁሉ እውነትና ከእውነት ጋር የተስማማ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገሩት ነገሮች ሁሉ በእርግጥ የተፈፀሙና የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ በታሪክ ውስጥ እና በሳይንሳዊ ምርምርም በአርኪዎሎጂም ሁሉ እውነትነታቸው በትክክል ተመስክሯል፡፡ የቁርአንን አባባሎች እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥና እንደ መጽሐፍ ቅዱስም በማስረጃ ማስደገፍ አይቻልም፡፡

እዚህ ነጥብ ላይ እኛ የምንናገረው ነገር ለትችትና ለክርክር ፍላጎት ኖሮን አይደለም፡፡ የእኛ ዋና ዓላማ የሰዎች ልጆች የዘላለም እውነትን እና ያንንም ሕይወት የሚያገኙበትን ትክክለኛ መንገድ መጠቆም ነው፡፡ በእርግጥም የሰው ሕይወት ፍፃሜ ከምንለው በላይ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ሕይወታችን በእውነት መሠረት ላይ ተመስርቶ በእውነት የማይመራ ከሆነ ፍፃሜያችን እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው የሚሆነው፡፡

እንግዲህ ቁርአን ከዚህ በላይ ያሉትን ነገሮችና ሌሎችም ብዙ ተመሳሳይ ነገሮችን በእግዚአብሔር ስም ዘግቦ ከሆነ፣ ስለለዘላለም ሕይወትስ የሚናገረው ነገር ምን ያህል እውነተኛ ነው ምን ያህል ይታመናል የሚለውን ልናስብበት ይገባናል፡፡

የአዘጋጆቹ ጥሪ፡-

የዚህ ድረ ገፅ አዘጋጆች ለአንባቢዎች ሁሉ የሚያቀርቡት ጥሪ ስለ ግል ሕይወታችሁ በትክክል  እንድታስቡበት ነው፡፡ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእግዚአብሔር የተዘጋጀው መንገድ አንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ይህም ለሰዎች ኃጢአት ይቅርታን ለማስገኘት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በሞተው በጌታ በኢየሱስ በኩል ወደ እግዚአብሔር የመግቢያ መንገድ መከፈቱን እንድታውቁና በግላችሁ ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ በመቅረብ ኃጢአታችሁን በመናዘዝ የኃጢአታችሁን ይቅርታ ከመሐሪው አምላክ እንድትጠይቁት ነው፡፡ አትዘግዩ ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ ኑ ይቅር ይላችኋል ይህንንም በግላችሁ እንድታውቁትና እርግጠኞች እንድትሆኑ ያደርግላችኋል፡፡ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ