ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነውን?

ብዙ ሙስሊሞች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እንደሆነ ለመቀበል ይከብዳቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢየሱስ አምላክ ሳይሆን ነቢይ ብቻ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ጌታ ኢየሱስ ግን ሰው የሆነ አምላክ ነው፡፡ ሰው የሆነውም በፈቃዱና ለሰዎች ካለው ፍቅር የተነሳ ነው፡፡

ስለዚህም ሙስሊሞች በጌታ ኢየሱስ ላይ የሚያነሱትን ጥያቄዎች በዚህ አምድ ስር በተከታታይ እንመለከታለን፡፡ በቅድሚያ ጥያቄዎቹን ቀጥሎም መልሶቹን እናያለን፡፡  

ጥያቄ አንድ መልስ አንድ

ኢየሱስ አምላክ አይደለም ሊሆንም አይችልም፣ ኢየሱስ እራሱ አንድም ጊዜ እንኳን እኔ እግዚአብሔር ነኝ አላለም፣ መጽሐፍ ቅዱስም ላይ እርሱ አምላክ ነው የሚል ጥቅስ የለም እናንተ ክርስትያኖች ናችሁ አምላክ የምትሉት ትክክል ስለዚህ ትክክል አይደላችሁም የሚል ጥያቄ ነው፡፡

ይህን ጥያቄ በተለየ መንገድ እንደሚከተለው ለማቅረብ እንችላለን፡

በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ደግሞ ደጋግሞ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ሲል የቆየ ሲሆን አዲስ ኪዳን ውስጥ ግን ኢየሱስ አንዴም እንኳን እኔ እግዚአብሔር ነኝ አላለም፡፡ የብሉይ ኪዳኑ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ሲናገር ኢየሱስ አንድ ጊዜም እንኳን አለመናገሩ በተለይም ኢየሱስ ለክርስትና እምነት በጣም ጠቃሚ ሆኖ እያለ ይሄ ያልሆነው ለምንድነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ሁለት መልሶች አሉት

አንደኛ፡ ጌታ ኢየሱስ ሰዎች በሚገባቸው መልክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሏል

ሁለተኛ፡ ጌታ ኢየሱስ በቀጥታ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ማለቱ በጊዜው ከሚያስከትለው ችግር የተነሳ አላለም

ሁለቱንም መልሶች ቅደም ተከተል በመስት እንመለከታቸዋለን

አንደኛ፡ ጌታ ኢየሱስ እኔ ሰዎች በሚገባቸው መልክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሏል፣

ይህንን ለማየት የምንነሳው ጌታ ኢየሱስ ከተናገራቸው ነገሮች ተነስተን ነው፣ እዚህ ላይ እኔ የምጠቅስላችሁ ጥቅሶች ከዮሐንስ ወንጌል ላይ ያሉትንና የሰሙት ሰዎች ውስጥ የፈጠረውን ነገር በመጥቀስ ነው

·        አንደኛው ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ንግግር ዮሐንስ ወንጌል 3.13 13 ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው። ይህ የትርጉም ችግር አለበት ቃሉ ከግሪኩ የሚለው በሰማይ ያለው ነው፣ አሁን በምድር የምታየው አሁን በሰማይ ያለውን ነው

ኒቆዲሞስ ዓይኑን ማመን ያቃተው ቢመስልም የሚያየው ሰው የሆነ እግዚአብሔር እንደሆነ ገብቶታል፣ ጌታ ኢየሱስ እየተናገረ ያለው እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ አሁን እዚህ የምታየኝ ሰው አሁን እያየኸኝ  እያለ በተመሳሳይም ሰዓት የምኖረው በሰማይም ነው እያለ ነው፡፡

ጌታ ኢየሱስ ለዶክተር ኒቆዲሞስ ማለት ትችላላሁ እያለው ያለው አሁን አንተ የምትመለከተው በሰማይም በምድርም ያለውን በገዛ ፈቃዱ ሰው የሆነውን አምላክ ነው፣  

·        ሁለተኛ፡ አባቴ ይሰራል እኔም እሰራለሁ

17 ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። 18 እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ዮሐንስ 5.17-18

ጌታ ኢየሱስ በዚህ ክፍል የተናገረው እኔም እንደ አባቴ እሰራለሁ ሲሆን፣ በጊዜው ይሰሙ የነበሩት የሃይማኖት አዋቂዎችና ስለ ሃይማኖትም ተቆርቋሪዎች ናቸው፡፡ እነርሱ የገባቸው ነገር በቁጥር 18 ላይ እርሱ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንዳለ ነበር፡፡  

·        ሦስተኛ፡ ከአብርሃም በፊት ነበርሁ  

ዮሐንስ 8.56-58 ውስጥ ጌታ ኢየሱስ የሚከተለውን ተናገረ፡፡ 56 አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው። 57 አይሁድም። ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት። 58 ኢየሱስም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው።

የሃይማኖት አዋቂዎች የነበሩት ፈሪሳውያኖቹ፣ ከቁጥር 56 ላይ የገባቸው ነገር ጌታ ኢየሱስ እኔ ከጥንት የነበርሁ ፈጣሪና ለአባታችሁ አብርሃም ቃል ኪዳን የሰጠሁ ነኝ እያለ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ፈሪሳውያኖቹ ግራ እንደተጋቡ መመልከት የምንችለው በቁጥር 57 ላይ ነው፣ ሆኖም ጌታ ኢየሱስ በግልፅ ያላቸው የናንተ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ በማለት ነበር፡፡

ውጤቱ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ዓይነት ነበር፣ በቁጥር 59 ላይ ግን፣ ፈሪሳውያኖቹ ድንጋይ አንስተው ሊወግሩት እንደፈለጉ ግልፅ ና ምክንያታቸው ደግሞ አንተ ሰው ሆነህ አምላክ ነኝ ትላለህ ነበር፡፡ እነርሱ ይገባቸው የነበረው ነገር እርሱ በግልፅ እኔ አምላክ ነኝ ይል እንደነበረ ነው፡፡ እርሱ ሰውን ለማዳን በፈቃዱ የሰውን ስጋ የለበሰ አምላክ ነው፡፡ አንባቢ ሆይ ድንጋይ እያነሱ ሊወግሩት እየፈለጉ ለምን አልወገሩትም ነበር?  መልሱ እርሱ አምላክም ስለሆነና ያለፈቃዱ ማንም ሊወግረው ስለማይችል ነበር፡፡

·        አራተኛ፡ ከእኔ ማንም አይነጥቃቸወም

28 እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም።  29 የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። 30 እኔና አብ አንድ ነን። 31 አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ። 32 ኢየሱስ። ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው። 33 አይሁድም። ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት።

ቁጥር 30 ላይ እኔና አብ አንድ ነን በማለቱ ከቁጥር 28 እስከ 29 ባለው ሁሉ ላይ ጌታ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን እየተናገረ ነው፣ ስለዚህም በድንጋይ ሊወግሩት ድንጋይን አነሱ፣ ጌታ ኢየሱስ ለምን ልትወግሩኝ ትፈልጋላችሁ ባለ ጊዜ ለራሱ የመለሱለት መልስ በጣም ግልፅና እርሱ አምላክ ነኝ እያለ መሆኑ ስለገባቸው እንደሆነ በቁጥር 33 ላይ መልሰዋል፡፡ የተናገሩትን ቃል በቃል ለመጥቀስ ያህል አንተም እራስህ ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለማድረግህ ነው በማለት ነው፡፡

የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች እራስህን አምላክ አድርገሃል በማለት የተናገሩት በትክክል ካዩትና ከሰሙት ነገር የተነሳ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ አምላክ ነኝ የሚል ባይሆን ኖሮ በድንጋይ ሊወግሩት አይነሱም ነበርና፡፡

·        አምስተኛ፡ ሰባቱ የጌታ ኢየሱስ እኔ ነኝ ሐረጎች

በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ሰባት ጊዜ እኔ ነኝ እያለ የተናገራቸው ነገሮች በሙሉ እርሱ አምላክ መሆኑን በአስደናቂ ሁኔታ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ማለትም እኔ አምላክ ነኝ ከማለት በምንም የማይተናነሱ አባባሎች ናቸው፣ እኔ ነኝ የሚለውን ቃል በመጀመሪያ የተናገረውና በዚህ ቃል እራሱን ያስተዋወቀው እራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እርሱም እራሱን የቻለ በማንም ላይ የማይደገፍ በማንም ምክንያት የማይኖር እራሱን የሚያኖር ብቻ መሆኑን እራሱን የሚጠራበት የራሱ አጠራር ነው፡፡

ሰባቱንም የእኔ ነኝ አባባሎች አሁን ለመተንነተን ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ ነው፣ እኔ ነኝ የሚሉት የጌታ ኢየሱስ አባባሎች ስታስቡ ማንም ነቢይ ወይንም ስጋ የለበሰ ይህንን ማለት እንደማይችል፣ የታወቀ ነገር ነው፡፡ ስለዚህም የብሉይ ኪዳን ግንዛቤ ያለው ሰሚ ሁሉ ጌታ ኢየሱስ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እያለ መሆኑን እንደሚረዳ ልትመለከቱ ትችላላችሁ፣ ቃሎቹም የሚከተሉት ናቸው፤  

·        እኔ ነኝ የሕይወት እንጀራ ዮሐንስ 6.35

·        እኔ ነኝ የዓለም ብርሃን ዮሐንስ 8.12

·        እኔ ነኝ በሩ ዮሐንስ 10.9

·        እኔ ነኝ መልካሙ እረኛ ዮሐንስ 10.11

·        እኔ ነኝ ትንሳኤና ሕይወት ዮሐንስ 11.25-26

·        እኔ ነኝ መንገዱ እውነቱና ሕይወቱ ዮሐንስ 14.6

·        እኔ ነኝ የወይኑ ግንድ ዮሐንስ 15.5

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን የተናገረባቸው እጅግ በጣም ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ ውስጥ ከዚህ በላይ የተቀመጡት አምስት ማስረጃዎች በሙሉ የሚያሳዩት የሰሙት ሁሉ እርሱ በግልፅ አምላክ ነኝ በማለት ይናገር እንደነበረ ነው፡፡

ጌታ ኢየሱስ በፈቃዱ የሰውን ስጋ የለበሰ አምላክ ሆኖ ከሰዎች አወላለድ በተለየ ሁኔታ የተወለደ አምላክ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በጤናማ አዕምሮ የሚያነብ ሁሉ የሚገነዘበው ነገር በሙሉ ጌታ ኢየሱስ ዝም ብሎ ነቢይ ወይንም ሰው ወይንም የሃይማኖት ጀማሪ እንዳልነበረና ነገር ግን የሰዎችን ልጆች ከዘላለም የእግዚአብሔር ፍርድ ለማዳን እራሱን የሰጠ አፍቃሪ አምላክ መሆኑን ነው፡፡

ከነዚህ እውነቶች የተነሳ ነው፣ በእርሱ የሚያምን የዘላለም ሕይወት ይኖረዋል ወይንም ይሰጠዋል የተባለው፣ በሌላ ነቢይ ያመነ የዘላለም ሕይወትና መንግስት የማግኘት መብት የለውም ይህ የሚቻለው በጌታ በኢየሱስ በማመን ብቻ ነው፡፡

የዚህ ዐምድ አዘጋጆች በተደጋጋሚ የሚያስተላልፉት መልክት፣ የዘላለም መንግስት ወይንም መንግስተ ሰማይ የመግቢያው ብቸኛው መንገድ አምላክ ሆኖ እያለ ስለ እያንዳንዳችን ፍቅር ሲል የሰውን ስጋ ለብሶ የመጣውን ጌታ ኢየሱስን በማመን በእርሱ የመንግስቱ ወራሽ እንድንሆን ነው፡፡

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቡ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ፍቅር ለመገንዝብ በንፁህ አዕምሮ እውነቱን ተመልከቱ በጌታም በኢየሱስ ክርስቶስ እመኑ የዘላለምን ሕይወት ትቀበላላችሁ፡፡ ጌታም ይርዳችሁ፡ አሜን፡፡